top of page
Search

ለትውልዱ ተስፋ


ከተለያዩ ሃገራት ወደ አሜሪካ ሃገር የተሻለ የኑሮና የስራ እንዲሁም የትምህርት ዕድልን ፍሉጋ ሲመጡ የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች እንዲህ የሚባሉ አይደሉም:: ወደዚህ አገር ሲመጡ ከቋንቋው ጀምሮ የሃገሬው ባህልና የአካባቢው የአየር ሁኔታው ሁሉ መጤውን የሚገዳደሩ ነገሮች ናቸው:: ከዚህ ቀደም በምንም አይነት ፈተና ቢያልፉም የዚህኛው ፈተና አይነትም ቢሆን በዋዛ የሚታለፍ አይደለም:: እንዳው ለተምሳሌነት የአሜሪካንን ሁኔታ አነሳሁ እንጅ ጉዳዩ በየትኛውም ሃገር የሚኖሩትን ሁሉ ይመለከታል:: ይህ ጉዳይ በተለይ በልጆቻቸው ላይ የበለጠ ተፅዕኖ ስላለው የነገሩን ውስብስብነት ከፍ ያደርገዋል:: እነዚህ ልጆች በሁለት የተለያዩ ባህሎች ማለትም በወላጆቻቸው የትውልድ ሃገራቸው ባህልና በአካባቢያቸው ባለው ልዩ ባህል መሃከል በመሆን በሁለቱም አቅጣጫዎች የመሳሳብ ውጥረት ውስጥ ማለፍ ግዴታ ይሆንባቸዋል:: ይህ ተፅዕኖ ደግሞ በተለይ ልጆቹ ወደ ጉርምስና የእድሜ ክልል ሲደርሱ በማንነታዊ ጥያቄዎቻቸው የሚነሱ የውስጥ ውዝግብ ደረጃ እጅግ ከፍ ይላል:: የአብዛኛውን የዲያስፖራ ችግር እኔም ከአመታት በፊት ወደ አሜሪካ ምድር ከመጣሁበት ግዜ ጀምሮ ያለፍኩባቸው ስለሆኑ ለመረዳት አያዳግተኝም:: ኑሮዬን በዚህ ሃገር ማድረግ ከጀመርኩበት ግዜ ጀምሮ ውስጤ የሚሰብር ነገር ቢኖር እነዚህን የዲያስፖራ ልጆች በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ መመልከት ነበር:: እነዚህ ልጆች በዚህ ሃገር የተወለዱ ናቸው አልያም ከህፃንነታቸው ጀምሮ ያደጉበትና ብዙውን የእድሜያቸውን ክፍል ያሳለፉበት ቦታ ነው:: በአብዛኛውን ማለት ይቻላል የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንግሊዘኛ ወይንም የተወለዱበትን ሃገር ቋንቋ ነው የሚሆነው:: ከአንድ ቋንቋ በላይ ተናጋሪ መሆን ከቻሉ ጥቅሙ የላቀ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ሳልገልፅ አላልፍም:: ስለወላጆቻቸው ባህልና ታሪክ ማስታወቅ እዚህም ሃገር ሆነ በሌላው አገራት ለተወለዱ ልጆች የማንነታቸው አሻራና ኩራታቸው ነው:: ወላጆቻቸው የኖሩበት የባህል ሁኔታ ወላጆቹ እራሳቸው በተወለዱበት ሃገር እጅግ የሚያስኬድ መሆኑ ግልፅ ነው::ሆኖም ግን እነዚህን ልጆች ከተወለዱበት ሃገር ባህል በተለየ በወላጆቻቸው ባህልና ዘዬ በግዴታ ኑሩ ማለት እጅግ አደገኛ አካሄድ ይሆናል:: ይህ ጉዳይ ከራሴ የግል ህይወት ጋር ትስስር ስላለው በድፍረት ለመናገር ይረዳኛል:: የበኩር ልጄ ጆሳያ እንደ ዲያስፖራ ልጅነቱ ወደፊት ሊታገላቸው ያላቸውን ነገሮች ለመረዳት አልዳገተኝም:: ገና በህፃንነቱ በእቅፌ ሆኖ የሚያሳሱ አይኖቹን ስመለከትና ስለወደፊት የህይወት ጎዳና ሳስብ ልቤ በመቃተት ይሞላል:: በውስጤ ያለውን መቃተት በቃላት መግለፅ ባልችልም ነገር ግን ሐዋርያው ዻውሌስ በሮሜ መፅሃፍ ላይ የተናገረው ቃል ወደ ውስጤ መጥቶ ያፅናናኛል:: "ወደ ሮሜ 8 26፤ እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል።" ስለዚህም ልጄንም ሆነ እኔን እራሱ ወደፈጠረ አምላክ በመፀለይና በመቃተት ስለ ወደፊት ህይወቱ አሳስባለሁ:: ወድያው ታማኝነቱና መልካምነቱ ውስጤን አርስርሰው ያፅናኑኛል:: የሚያስፈልጉንን ነገሮች ከእኛ በላይ እንደሚያውቅና ደግሞም እንደሚሞላብን በቃሉ ይነግረናል:: እግዚአብሔር በበረታቹ ክንዱ እኔንም ሆነ ሌሎች ውድ ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቼን እንዴት እንደተሸከመን ልጄ እንዲያውቅ እርሱም ደግሞ ያንን ልምምዱ እንዲያደርገው የዘወትር ምኞቴና ስራዬ ነው:: ነገር ግን ውስጤ ከከበዱኝ ጉዳዮች መሃል የነገ የዲያስፖራው ልጆች የቤተክርስቲያን ተረካቢነት ስጋት ነው:: የስንቶቻችን ልጆች ናቸው ስላለፈውና ስላለው የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን መነሻን አውቀውና አደራን ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ? ለልጆቹ መንፈሳዊ ነገር አግባብ ያለው ትኩረት መስጠት ካልተጀመረ ወይንም በአንዳንድ ቦታዎች እንደሚታየው የተለየ ክፍል ብቻ ተሰጥቷቸው ተገለው እንዲማሩ ብቻ ማድረግ ስላለፈውና ስለ አሁኑ የቤተክርስቲያን የአደራረግ ሁኔታን አውቆ ነገን የሚረከብ ትውልድን ማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል:: በእርግጥ ወንጌልን በእንግሊዝኛ አልያም በሚገባቸው ቋንቋ ለብቻቸው እንዲማሩ ማድረግን እጅግ የማበረታታው ሃሳብ ነው:: ነገር ግን ተገለው ብቻ "የእኛ እና የእናንተ" በሚል ተአስቦ የሚኬድበት አካሄድ ተረካቢን ያሳጣናል:: ባጠቃላይ ማለት ይቻላል በሌላ ሃገራት የሚደረጉ ጉባዔዎች ሁሉ በአማርኛ ቋንቋ ብቻንእንደሆኑ በሚገባ አድርጌን አውቃለሁ:: ለብዙዎቻችን ወላጆች በእንግሊዝኛው አልያም በሌላ ቋንቋ ማምለክ ብዙ ምቾት እንደማይሰጠንም እረዳለሁ:: ነገር ግን እያንዳንዳችንን ወደ መንግስቱ እንደ ቤተሰብ ከጠራን በፊቱም ለአምልኮ ስንቀርብ እንደቤተሰብ አንድ ላይ ሊያየን ይወዳል:: ነገር ግን ብዙዎቻችን ባለማስተዋልም ሆነ በግዴለሽነት ቤተክርስቲያን ከገባንበት ሰዓት እንስቶ እስክንወጣ ድረስ በእራስ ወዳድነትልጆቻችንን በሌላ ክፍል እንዲማሩ ብቻ በመተው የእኛን የአምልኮ መጠማትና ፍላጎ ብቻ ላይ እናተኩራለን:: በዚህ ሁኔታ ልጆቻችን እያጡ ያሉትን ቁም ነገር ለመግለፅ ከቂላት ያለፈ ነው:: ስለዚህም እራሳችንን ልንጠይው የሚገባን ነገር ቢኖር ለእነዚህ ችግሮች ሁሉ ውጤታማ በሆነ መንገድ መፍትሄ እንዴት እናበጅላቸው? በግሌ ለእንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት ባልችልም ለውይይት ይቀርብ ዘንድ ጥቂት ሃሳቦችን ለማበርከት ይኸው ተነስቻለሁ:: እኔ በግሌ በቤተክርስቲያን ውስጥ ካሉ የአገልግሎት ዘርፎች መሃል የህፃናትና የታዳጊ ወጣቶች አገልግሎቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ነኝ:: ይህንም የምልበት ዋንኛ ምክንያት የቤተክርስቲያንም ሆነ የወንጌል የነገ ቀጣይነት የተመረኮዘው በተረካቢው ትውልድ ዝግጅት ላይ ነው:: ትላንት ተጀምሮ ዛሬ ደግሞ የያዝነው ነገ ላይ ሊቀጥል የሚችለው በተረካቢዎች ላይ በሙሉ አቅማችን ስንተጋ ብቻ ነው:: ከምንም ነገር በላይ መዘንጋት የማይገባን ነገር ቢኖር በእግዚአብሔር ዘንድ የተአማኝነትን ፀጋ አግኝተን ከእርሱ ዘንድ ልጆችን እንደ ስጦታ ልናሳድጋቸው ስንቀበል መብልና መጠጣቸውን ለማሟላት ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊም ነገር አንፀን እንድናሳድጋቸው ነው:: ሙሴ ከማለፉ በፊት ለእስራኤላውያን ቀዳማዊውን ነገር አስተምሯል:: “ኦሪት ዘዳግም 6: 6፤ እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። 7፤ ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።” አንድ የማምነውና አማራጭ የሌለው ነገር ቢኖ ስለልጆቻችን የነገ ህይወት ሲባል በሌሎች ነገሮች ዋጋ እንደምንከፍለው ሁሉ በመንፈሳዊውም ጉዳይ ላይም ዋጋ መክፈል ይኖርብናል:: በእርግጥ አብዛኛዎቻችን ወላጆች እንግሊዘኛም ሆነ ሌሎች ቋንቋዎች አፋችንን ስላልፈታንባቸው አንደሚያስቸግረን አጥብቄ እረዳለሁ:: በዚህም ምክንያት እራሳችንን በድግግሞሽ ስህተት ውስጥ እናገኘዋለን:: ነገር ግን እራሳችንን መንፈሳዊነትን በትውልድ ቋንቋችን ብቻ በመገደብ ልጆቻችንንም በተወሰነ የአጥር ክልል ብቻ እየገደብናቸው እንገኛለን:: ቢያንስ ስለ ተረካቢ ልጆቻችን ሲባል ብቻ ጉባኤዎቻችንና አምልኮዎቻችን ከአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሊዘሉ ይገባቸዋል:: አምላካችንና ጌታችን ኢየሱስን በአማርኛና በአገሩ ቋንቋ ልናመሰግንና ልናመልክ ይገባናል:: ስለሆነም ልጆች ቢያንስ በአምልኮ ሰአት ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን ወደ እግዚአብሔር ፊት የመቅረብ እድል ያገኛሉ:: በየቤቶቻችን ከልጆቻችን ጋር በማዕድ ጊዜ አብረን እንጀራን እንደምንካፈል ሁሉ በአምልኮ ሰዓትም የእግዚአብሔርን ህልውና በአምልኳችን ውስጥ እንካፈላለን:: ከዚህ የሚበልጥ እድል የለም:: ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በህብረት ሲያመልኩ እርስ በእርሳቸው የመሳሳብና የመዋደድ እንዲሁም የመከባበር ባህል ይጎለብታል:: ጉባዔዎቻችንን በዚህ መልኩ ሁሉን አሳታፊ ስናደርጋቸው በልጆቻችን ልብ ውስጥ ለትምህርታቸውና ለጤንነታቸው ለሌሎችም ጉዳዮቻቸው ትኩረት እንደምንሰጥላቸው ሁሉ በመንፈሳዊ ህይወታቸውም ስኬትን እንደምንናፍቅላቸው ይገባቸዋል:: ምን አልባት በዚህ ሃሳብ ላይ የተቃውሞ ሃሳብ ያለው ቢኖር ሃሳባችሁን ከመሰንዘራችሁ በፊት ይህን ጥያቄ ከግምት አስገቡት:: ለመሆኑ ብዙ መረዳት በማትችሉበት ቋንቋ ጉባዔ ውስጥ እራሳችሁን ብታገኙት ምን አይነት ስሜት እንደሚሰማችሁ አስቡት:: ምቾት ይኖራቹሃል? የቤተኝነት ስሜት ይደማቹሃል? ታድያ እንዴት ነው የገዛ ልጆቻችን በሚገባ በማይረዱበት ቋንቋ ጉባዔን ሊካፈሉ የሚችሉት? ስለ ስላለፉ የቤተክርስቲያን ታሪኮቻችንና ስለ ወንጌላችን ሊገባቸው በሚችለው ቋንቋ ዘይቤ ልናስተላልፍ ይገባናል እላለሁ:: ቋንቋ መሳርያ እንጅ ሃይማኖት እንዳልሆነ ተረድተን ዋናው ቁም ነገር የሚተላለፈው ነገር እንጂ የምናስተላልፍበት መሳርያ አይደለም:: ጉባዔዎቻችንን በተለያዩ ቋንቋዎች ማድረጉ ጥቅሙ ብዙ ነው:: ሌላኛው ጥቅም ልጆቻችን በውስጣቸው ያለውን ስጦታ ተረድተው በዚያ ነገር እንዲያድጉና ለተረካቢነት ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል:: በተጨማሪም ስላለፈውና ስለአሁኑ የቤተክርስቲያን ራዕይ በይበልጥ በቀላሉ ተረድተው ለወደፊት እንዴት መጏዝ እንዳለባቸው ለመረዳት መንገዱ ጥርግ ይሆንላቸዋል:: ጉባዔዌቻችን በህብረ ቋንቋዎች ሲደምቁም የህብረትና የመቀባበል መንፈስ ይጎለብታል:: የዚህ አይነት አካሄድ የሐዋርያው ዻውሎስን መልክት በሚገባ ያንፀባራቃል:: "ወደ ኤፌሶን 2 14-15፤ እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥" ይህን የእርሱን ሰላም የምንካፈል ከሆነ ዘንዳ ትንሽ መስዋእትነትን መክፈል ይጠበቅብናል:: ልጆቻችንም ለእነርሱ ስንል የምንከፍለው ዋጋ መሆኑን መረዳት አይዳግታቸውም ይህንንም በእርግጥ ያከብሩታል:: የጉባዔዌቻችን ይዘት በእንደዚህ አይነት ማለትም በአማርኛና በሃገሩ ቋንቋ የታጀበ ሲሆን ልጆቻችን በወንጌል ትጥቅ በሚገባ ታጥቅው ለሚያገኟቸው ጏደኞቻቸው ሁሉ ወንጌልን ለማካፈል ድፍረትንና ብቃትን ያገኛሉ:: ይህ ካልሆነማ እኛን የለወጠው ወንጌል እንዴት እነሱን ለውጦ ከእነሱም አልፎ በእነሱ አማካኝነት ሌሎችን ሊለውጥ ይችላል? ወንጌልን የሚቀበሉበትን መንገድ ልናቀላቸው ይገባል:: በስተመጨረሻም ይመስለኛል መዘንጋት የማይገባን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ለአላማእ መጥራቱን ነው:: ኢየሱስ ደቀመዝሙራኑን ሲልክ ወደ አለም ሁሉ ሄደው ደቀመዝሙራን እንዲያፈሩ ነበር:: በስራ ቦታ የምናገኛቸውን የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጏደኞቻችንን እንዴት ነው በአማርኛ ጉባኤ ውስጥ ጋብዘን እውነትን የምናካፍላቸው? እግዚአብሔር እኛን ከትውልድ ሃገራችን አውጥቶ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሲያስቀምጠን በአላማ ነው:: ተልዕኮን ሰጥቶናል:: በውጪ ጎዳናዎቻችን የተጨናነቁት ነፍሳት ደራሽ የሚፈልጉ ናቸው:: የእኛን መገለጥ ፍጥረት በናፍቆት በመጠባበቅ ላይ ነው:: ስለዚህም ተረካቢውን ትውልድ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ማሳተፍ ተገቢ ነው:: ኢየሱስ በደሙ የጠራት ቤተክርስቲያን ለመሆን ከፈለግን በየአካባቢው ካሉ ከሌሎች ቋንቋ ተናጋሪ ቤተክርስቲያናት ጋር በመቀራረብ ለእግዚአብሔር መንግሥት በህብረት መስራት ያስፈልገናል:: "ወደ ገላትያ 3 28፤ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።" ይሄን ሸክም እግዚአብሔር በልቤ እንዲህ አስቀምጧል:: ይህ ቅናትና ጉጉት እንደ እሳት በውስጤ ይነዳል:: ብዙ ማድረግ ባልችልም በዚህ መልኩ ስጋቴንና የልቤን ሸክም በማጋራት ይህ ጉዳይ ይመለከተኛል ለምትሉ ሁሉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ:: ለወንጌል እውነት እንተባበር:: የልጆቻችንን የመንፈሳዊ ጤናማነት የተረጋገጠ ለማድረግ ሀዚህ ራዕይ እንተባበር:: ስለዚህ ይህ በውስጤ ያለው ራዕይ በተግባር ውሎ ፍሬን ያፈራ ዘንድ አገልግሎቴን በፀሎትና በተለያዮ መንገዶች ስትደግፉኝ ለነበራችሁ ሁሉ አሁንም በፀሎታችሁና እግዚአብሔር ባሳሰባችሁ ነገር ሁሉ አብረን እንድንሰራ ጥሪዬን አቀርባለሁ:: ስለዚህም በእኛ አንድነት እግዚአብሔር ደስ ይለው ዘ

ንድ:: ሁሉ አንድ ይሁን!




9 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page